የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ !!
በፓርቲያችን ፕሮግራም ላይ በግልጽ እንደተመለከተው የብልጽግና ፓርቲ ጥቅል ዓላማ ፥’የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ’ ነው፡፡
ብልጽግና ስንል ፈርጀ ብዙ ትርጓሜን ያዘለ ነው፡፡ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ ገጽታ አለው።
የኢኮኖሚ ብልጽግና የሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች በተገቢና በዘላቂነት ለማሟላት የሚያስችል ፈጣን እና ሁለንተናዊ ዕድገትን በማስመዝገብ፣ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ያለው ኢኮኖሚ በመገንባት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና የሕዝብን ድህነትና ኋላቀርነትን ለመቅረፍ መቻልን ያካተተ ነው።
የፖለቲካ ብልጽግና ስንል ለዴሞክራሲ ባህል ማበብ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን በመገንባት፣ የሕዝቦች ነጻነትና እኩልነት ተረጋግጦ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረውላቸው የሚኖሩባት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተረጋገጠ፣ ፌዴራላዊት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ጽኑ መሠረት ላይ ማቆም ነው።
የኢኮኖሚ ብልጽግና ስንል ደግሞ የሕዝባችን ሰፊ ክፍል የሆነውን አርሶ አደር፣ ወጣት፣ ሴቶች እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ማዕከል ያደረገ አካታች የኢኮኖሚ ሥርዓት በመገንባት የሕዝባችንን የጋራ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ዓላማ ይኖረዋል።
በተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ የግሉን ዘርፍና ሌሎች የኢኮኖሚ ተዋናዮችን ተሳትፎ በማጎልበት ምርታማነትን በላቀ ደረጃና ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚያሳድግ እንዲሆን ያደርጋል።
በዚህም መሠረት ፓርቲያችን ጥራት ያለውና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት እንዲሁም ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋገጥ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት ሀገራችንን ወደ ብልጽግና ጎዳና ለማሸጋገር ያልማል።
ማኅበራዊ ብልጽግና ማለት ደግሞ መልካም ሀገራዊ ወጎችን፣ ዕሴቶችን እና ባህሎችን በማዳበር በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ማፍራት፣ በአካልና በአእምሮው የዳበረ ጤናማ ዜጋ መፍጠር፣ ከአስከፊ ማኅበራዊ ችግር የተጠበቀ ኅብረተሰብ መገንባት እና በሕዝቦች መካከል አዎንታዊ ሰላም በመፍጠር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ የፓርቲያችን ጥቅል ዓላማዎች ናቸው።
