
(ኢ.ፕ.ድ)
የአሁኑ ትውልድ ያለፉ ችግሮችን በማንሳት ከመወቃቀስ ወጥቶ ለቀጣይ መፍትሄ ማስቀመጥ በሚያስችሉ አጀንዳዎች ዙሪያ አተኩሮ መስራት እንዳለበት የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ተናገሩ።
”አካታች ብሄራዊ ምክክሩን ከማሳካት አንፃር የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሃሳብ ሚኒስቴሩ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ተጀምሯል።
የምክክር መድረኩ ሲጀመር ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ዓመታት የመጠላለፍና የመነቃቀፍ ፖለቲካ ሲካሄድ ቆይቷል።
በዚህም የዜጎች የሰላም እጦት፤ ተረጋግቶ ያለመኖር እና ለበርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
ይህንኑ የመነቃቀፍና የመጠላለፍ ፖለቲካ ለማስወገድ የአሁኑ ትውልድ ያለፉ መጥፎ ታሪኮችን በማስታወስ መቆዘም ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ መፍትሄ ሊሆን በሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት መንግስታት ዴሞክራሲን ለይስሙላ ሲጠቀሙ በመቆየታቸው በሃገሪቱ የዳበረ ዴሞክራሲ መገንባት አለመቻሉን አውስተዋል።
አሁን ላይ ህዝቡን በጋራ ሊያግባባ የሚችል ብሄራዊ አካታች ምክክር በማስፈለጉ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ መላ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን በጎ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል ነው ያሉት።
ብሄራዊ ምክክሩ ቢቻል ሁሉንም ሊያግባባ በሚችል አግባብ እንደሚከናወን ገልጸው፤ አሊያም ለቀጣዩ መልካም የስርዓት አቅጣጫ ቀይሶ ማለፍ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ለዚህም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ዘመኑን የሚመጥን ሃሳብ በማፍለቅና አቅጣጫዎችን በማሳየት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አቶ ብናልፍ አመልክተዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዘውዱ እምሩ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የውጭ ጠላት ወረራን በድል ልትወጣ የቻለቸው ከብሄርና ከዘር የፀዳ ፅኑ ብሄራዊ አንድነት በመኖሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የውጭ ጠላት የቱንም ያህል ቢጥር የውስጥ አንድነት ጠንካራ እስከሆነ ድረስ ተፅዕኖ ሊፈጥር አይችልም ብለዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጰያ ላለችበት ሁኔታ የውስጥ አንድነት ከመላላ ጋር ተያይዞ የመጣ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ጠንካራ ብሄራዊ አንድነት መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ፤ በምክክር መድረኩ የሰላም ሚኒስቴርና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራሮች እንዲሁም ምሁራን፣ ተማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን በምሁራን እየቀረቡ ባሉ ጥናታዊ ፅሁፎች ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።









