የብልጽግና ፓርቲ የመጀመርያው ጉባኤ የአቋም መግለጫ ሙሉ ቃል

Ethiopia | ከፈተና ወደ ልዕልና

የብልጽግና ፓርቲ የመጀመርያው ጉባኤ የአቋም መግለጫ
ፈተናዎችን ተሻግረን የኢትዮጵያን ልዕልና ማብሰር እንደምንችል በመተማመን ቅድመ ጉባኤ ጥልቀት ያለው ውይይት በአዳማ አደርገናል፡፡ ከየካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ሲከናወን የቆየው የመጀመርያው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ በስኬት ተጀምሮ በስኬት መጠናቀቁ ወትሮም ቢሆን ገና ከጅምሩ አቅዶ መፈጸም ጀምሮ መጨረስ ቋሚ ባህል አድርጎ ለተነሳው ፓርቲያችን ስኬታማ ድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

ሀገራዊ ለውጡ ከተጀመረ አራተኛ አመቱን የያዘ ቢሆንም ባለፉት አመታት በርካታ የሆኑ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኩነቶች ተስተናግደዋል፡፡ እንቅፋትን እንደድልድይ ተጠቅሞ ወደዘላቂ ብልጽግና ለመንደርደር የተደረጉ ጥረቶች ሁሉ ከሞላ ጎደል ተሳክተዋል፤ ወደፊትም የተለያዩ ተሞክሮዎች እየታከሉባቸው ለታላቅ ስኬት መንደርደርያ ይሆናሉ የሚል እምነት ተይዟል፡፡

ከብልጽግና ፓርቲ ምስረታ ጀምሮም በርካታ የምንኮራባቸው ድሎች ያስመዘገብን ቢሆንም በተመሳሳይ ጉድለቶቻችንና ተግዳሮቶቻችንም ቢሆኑ በቀላሉ የምናያቸው አይደሉም፡፡በመጀመርያው ጉባኤያችን ሰፊ ጊዜ ሰጥተን ለማየት የሞከርነውም ባለፉት አራት አመታት የነበሩንን መልካም ተሞክሮዎች እንዴት እናስቀጥል፣ ጉድለቶቻችንስ በምን መልኩ እንቅረፍ፣ ተግዳሮቶቻችንን በመቋቋም እንዴት እንሻገር ስንል ሰፊ ውይይት እና ምክክር አድርገናል፡፡

በአዳማው ውይይታችን ያሳለፍናቸውን ጊዚያት ካስቀመጥናቸው ትልሞች እና ግቦች በመነሳት በሰፊው የገመገምን ሲሆን በተለይም የአገረ መንግስት ግንባታ ጉዟችንን በጥልቀት ፈትሸናል፡፡ አገር የማጽናት ከትውልድ ወደትውልድ የማሻገር ትልማችን ሊሳካ የሚችለው ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በጽኑ ኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ በመትከል እንደሆነ አምነን ከዚህ በመነሳት የምንገኝበትን ሁኔታ በቂ ጊዜ ወስደን ለማየት ሞክረናል፡፡

ምንም እንኳን ከሰላም እና ጸጥታ መደፍረስ ከዜጎች መፈናቀል እና ሞት ጋር በተያያዘ ያጋጠሙን ጉድለቶች ቀላል ተደርገው የሚወሰዱ ባይሆንም በአንጻሩ አገር ወዳድ ዜጎች በመፍጠር ለዜጎች ሁለንተናዊ ክብር እና ዘላቂ ሰላም የሚተጋ መንግስታዊ መዋቅር እና ተቋማዊ ሪፎርም ለማረጋገጥ የሰራነው ስራ ከፍ ያለ ትርጉም የሚሰጠው ነው፡፡

ከፈተና ወደልዕልና በሚል መሪ ቃል በጥብቅ ዲሲፕሊን የተመራው የአዳማው ውይይት ለመጀመርያው ጉባኤያችን በስኬት መጠናቀቅ የማይተካ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ከአሁን ቀደም ከተለመደው የውይይት አካሄድ ወጣ በማለት ለጉባኤው አጀንዳዎች በቂ ጊዜ በመመደብ ዴሞክራሲያዊ አሳታፊነትን በተሟላ መንገድ ለማረጋገጥ ሰፊ ጥረት የተደረገ ሲሆን በጉባኤው አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት መክሮ ወደተቀራራቢ አመለካከት ለመምጣት አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

የብልጽግና ምስረታ፣የተቋማት ግንባታ፣ ስኬታማ ምርጫ በማካሄድ በህዝብ ዘንድ ቅቡልት ያለው መንግስት መመስረት መቻላችን፣ አረንጓዴ አሻራችንን መሬት ለማስነካት የሄድንበት ርቀት፣ ለብዝሀ ኢኮኖሚ ልማት የሰጠነው የተለየ ትኩረት፣በከተማ እና በገጠር ልናከናውናቸው የሚገቡ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎቻችን፣የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነትና የቀጠናው ትብብር፣ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አፈጻጸምና የተገኘው ስኬት፣የውስጠ ፓርቲ ስራችን አጠቃላይ ሂደት እና ውጤቱን በስፋት በመዳሰስ ጥልቀት ያለው ውይይት የተደረገ ሲሆን በጉባኤው ተሳታፊዎች በኩል ተጨማሪ ግብአት የተገኘበትና ትምህርት የተወሰደበት ነበር፡፡

የጉባኤው ሂደት እና ነጥረው የወጡ ዋና ዋና ጉዳዮች
ስኬቶቻችን በርካታ እና ስፋት ያላቸው ቢሆኑም ያጋጠሙን ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶችም በእጅጉ የተወሳሰቡ እና ረዥም እና አድካሚ ተገዳዳሪ ሁኔታ የፈጠሩብንም እንደነበሩ አመላክተናል፡፡ ከውስጣዊ ፈተናዎቻችን ስንነሳ አልጠግብ ባዩ ጁንታ በሁሉም አቅጣጫ የፈጠረብን እንቅፋት የህዝባችንን አኗኗር በእጅጉ ያወሳሰበው ከመሆኑም በላይ በአገረ መንግስቱ ቀጣይነት ላይ የህልውና ስጋት እስከመሆን የደረሰ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ህዝባችንን ዋነኛ አቅም አድርገን በመጠቀም የተቃጣብንን የህልውና አደጋ በብቃት መመከት ችለናል፡፡

ጽንፈኝነት የወለደው አገራዊ ፈተናም ቢሆን ፖለቲካው እንዳይሰክን በማድረግ በኩል አሉታዊ ሚና ነበረው አለውም፡፡ አለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታውን ተከትሎ የተፈጠረው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት እና የተፈጥሮ አደጋ በተለይም ኮሮና አንበጣ እና ድርቅ የፈጠሩት አሉታዊ ጫና በማህበረሰቡ አኗኗር ላይ ቀጥተኛ እና የወዲያው ተጽዕኖ የፈጠረ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የኑሮ ውድነት እና የተረጋጋ የገበያ ሁኔታ አለመፈጠር በብልጽግና ጉዟችን ሁነኛ እንቅፋት እንደሆነ ተመልክተናል፡፡

ባሳለፍናቸው አመታት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን እና የአንደኛና እና የሁለተኛ ዙር ውሀ ሙሌትን ተከትሎ እንዲሁም ከህልውና ትግላችን ጋር በተያያዘ የተፈጠረብን የውጭ ጣልቃ ገብነት በእጅጉ የተፈተንበት ጉዳይ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ የውጭ ጣልቃ ገብነቱ የፈጠረብን ጫና በሀገራችንና በህዝባችን ላይ ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ተጽዕኖ እንደፈጠረ በውይይታችን ላይ ተመልክተናል፡፡

ከተፈጠረብን ጫና ባሻገር በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባደረጉት የጋራ እርብርብ በምሳሌነቱ ለአለም የሚተርፍ ታሪካዊ ድል የተቀዳጀንበት እንደነበረም እስታውሰናል፡፡

በውይይታችን ከተዳሰሱና የተለየ አጽንኦት ሊሰጣቸው ይገባል ብለን የተመለከትናቸው ነጥቦች ከህዝብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎች እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በተለይም ከሌብነት እና ከስርቆት ጋር ህዝባችንን ያማረሩ ጉዳዮችን በስፋት የገመገምን ሲሆን በሁሉም አካባቢ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችንም ለመመልከት ሞክረናል፡፡

በተለይም የህዝባችንን ኑሮ ከእለት ወደእለት አስቸጋሪ እና ውስብስብ እያደረገው የመጣውን እርስ በእርስ የመጠራጠር እና ያለመተማመን ችግር፣ መሰረታዊ የሆነ የገበያ ጉድለት እና የኑሮ ውድነት፣ መፈናቀል እና ሞት የሚቆምበትን ሁኔታ በጥልቀት ገምግመን ዘላቂ መፍትሄ የሚመጣበትን አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የውስጠ ፓርቲ ፖለቲካዊ ጤንነታችንን በቅጡ የተመለከትን ሲሆን አባላትን የማጥራት እና አመራር የማብቃት ስራችን የማያቋርጥ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ተግባብተናል፡፡

ከጉባኤው ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል ያለፉት አመታት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የኢንስፔክሽንና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርት ቀርቦ በጥልቀት የታየ ሲሆን በተጨማሪ የፓርቲያችንን ፕሮግራምና ህገደንብም በጉባኤው ተሳታፊዎች ተፈትሾና ተመርምሮ ጥልቅ ውይይት ከተደረገ በኋላ በርካታ የማሻሻያ ነጥቦች ታክለውበት ጸድቋል፡፡

የመጀመርያው የፓርቲያችን ጉባኤ እነዚህን መሰረታዊ አጀንዳዎች መርምሮ በሰፊው ከተወያየና ካጸደቀ በኋላ ከጉባኤ እስከ ጉባኤ ለቀጣይ ሦሥት አመታት ፓርቲውን በበላይነት የሚመሩ ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶችን፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን፣ የኢንስፔክሽንና ቁጥጥር ኮሚሽን አባላትንና የስራ አስፈጻሚ አባላትን ግልጽ፣ ነጻ፣ አሳታፊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምረጥ ችሏል፡፡

እኛ የብልጽግና ፓርቲ የመጀመርያ ጉባኤ ተሳታፊዎች በወሳኝ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት ተወያይተን የአገራችንን መጻዒ እድል በሚወስኑ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ በጉባኤያችን የተደረሱ ማደማደሚያወችንና የተቀመጡ አውራ አቅጣጫዎችን በኃላፊነት እና በተጠያቂነት ስሜት በመያዝ እስከሚቀጥለው ጉባኤ ድረስ እረፍት የለሽ አመራር የሚሰጡ የፓርቲውን የቀጣይ ዘመን መሪዎች መርጠናል፡፡ ስለሆነም የአገራችንንና የህዝባችንን ሁለንተናዊ ደህንት እና ጥቅም አክብሮ ማስከበር ከላይ እስከታች የሚገኘው የፓርቲያችን መዋቅር ግዴታ መሆኑን እያሳሰብን የሚከተለውን አቅጣጫ እና የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

1ኛ. የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በማስፋት እና በማጽናት የህዝባችንን ሁለንተናዊ ደህንነት ማረጋገጥ የፓርቲያችን ቀዳሚ አጀንዳ ነው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ የውስጠ ፓርቲ ጤንነታችንን መጠበቅ ከሌብነትና ከተደራጀ ስርቆት አንጻራዊ ነጻነቱን የጠበቀ የአመራር ስምሪት ማረጋገጥ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ የአገልጋይ አመራር ስብዕናን የተላበሰ ጠንካራ የፓርቲ መስተጋብር ለመፍጠር ወስነናል፡፡
ያለጠንካራ ፓርቲ ግንባታ እቅዶቻችንን ማሳካትም ሆነ የህዝባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስለማንችል ለዚህ ዘርፍ የተለየ ትኩረት የምንሰጥ መሆኑን እናረጋግጣለን፤ ለዚህም ቃል እንገባለን፡፡

2ኛ. የየአገራችንን አንድነት እና የህዝባችንን ሰላም በጽኑ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ መድረኩ የሚጠይቀንን እና አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ተዘጋጅተናል፡፡ ስለሆነም ለዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ለአገራዊ አንድነት ተጠናክሮ መውጣት፣ለዜጎች ክብር እና ነጻነት እንዲሁም በህይወት የመኖር መብት መረጋገጥ እና የአካል እና የንብረት ደህንነት መከበር በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መስራት እንዳለብን መተማመን ላይ ደርሰናል፡፡

ስለሆነም አገራዊ መግባባት ማምጣት የሚያስችል አካታች ብሄራዊ ምክክር በማድረግ በብዙ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ልዩነቶችን ማጥበብ የሚያስችል ፈጣንና መላውን ህዝብ ያሳተፈ ምክክር በማድረግ በህዝባችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ ዘላቂ እና የማያዳግም እምርታዊ ለውጥ እንዲመጣ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለብን መተማመን ላይ ደርሰናል፡፡ ስለሆነም በተባበረ ጥረት ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነትን በመገንባት፣በህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም መሰረት ላይ የታነጸ አገራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ ቃል እንገባለን፡፡

  1. በተጨባጭ ውጤት የሚገለጽ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ እውን እንዲሆን በጋራ መረባረብ አለብን፡፡የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም የበለጸገ አስተሳሰብ ውጤት እንጂ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሰለባ መሆን የለበትም፡፡ እርስ በእርስ አለመከባበር፣ መዘላለፍ፣ በአደባባይ ላይ ሳይቀር ጸያፍ ድርጊት መፈጸም፣ ለህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት እና ለእህትማማችነት የማይመጥን ጸረ አንድነት የሆነ ከፋፋይ ድርጊት መፈጸም የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ጸር እንደሆነ ጉባኤያችን ያምናል፡፡

ኢትዮጵያ የብዝሀነት አገር መሆኗ ግልጽ ሆኖ እያለ ከእኛ ይልቅ እኔብቻ በሚል ተነጣይ አስተሳሰብ መጠመድ፣ ሽማግሌዎችን እና የማህረሰቡን ጉልሀን መዝለፍ፣ የቡድን መብትን አለማክበር፣ ብዝሀነትን ማጣጣል፣ የመንግስት ሹመኞችን ከግብረገብነት ባፈነገጠ መልኩ ማንቋሸሽ ኢትዮጵያዊ ልማድ ካለመሆኑም በላይ ዴሞክራሲን የሚያቀጭጭ ኋላ ቀር ድርጊት በመሆኑ ድርጊቱን የሆነ ቦታ መግታት ካልቻልን አገራችንን ብዙ አመት ወደኋላ የሚጎትት እና በውጥን የሚያስቀረን የብልጽግና ጉዟችን እንቅፋት ነው፡፡

እርስ በእርስ በመቻቻል እና በመከባበር፣ ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር እምርታዊ ለውጥ በማምጣት አገራችንን ወደፊት ሊያስፈነጥር የሚችል የተግባቦት ስራ መስራት ይኖርብናል፡፡የፍትህ አካላት ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የሚኖራቸውን አበርክቶ አስፍተውና አልምተው መተግበር አለባቸው፡፡ ለዚህም በጋራ መታገል ይኖርብናል፡፡ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ በአንድ ወገን ጥረት ብቻ የሚሳካ አይደለም፡፡

ሌብነትን የማይሸከም አሰራር እና ፖለቲካዊ ከባቢ መገንባት የሁላችንም ግዴታ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ስለሆነም ከመላው ህዝባችን ጋር በመተባበር እና በመቀናጀት አገር በቀል እሴቶቻችንን በመጠበቅና በመንከባከብ፣ እርስ በእርስ በመከባበርና በመቻቻል በጅምር ላይ የሚገኘውን የአገራችንን ዴሞክራሲ የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ ቃል እንገባለን፡፡

4ኛ. ኢኮኖሚያዊ መልሶ ማቋቋምና የአስር አመት ዕቅድ ትግበራ ስራችን ላይ ፈርጀ ብዙ ስራ በመስራት የአገራችንን ኢኮኖሚ ማሳደግ፣ የህዝባችንን የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲጨምር ማድረግ በአጠቃላይ የህዝባችንን ኑሮ አሁን ከሚገኝበት ሁኔታ ማሻሻል አለብን፡፡

አፋጣኝ መፍትሄ በሚሹ ጉዳዮች ላይ ፈጣን እርምጃ መውሰድ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ ምንም እንኳን የአለም አቀፍ ሁኔታው ለገበያ ጉድለት መፈጠር የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ቢኖረውም ወቅታዊ የሆነውን የህዝባችንን የኑሮ ውድነት ችግር ለማሻሻል ያላሳለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለብን እናምናለን፡፡

የመሰረታዊ ሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦት ችግር፣ የኑሮ ውድነት፣ በገቢና በወጭ ምርት ላይ የሚታይ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ የስራ አጥነት ችግር በዘላቂነት የሚፈታበትን ትልም ከወዲሁ ቀይሶ የህዝባችንን ሸክም ማቃለል እንዳለብን በጉባኤው ተመላክቷል፡፡

በገጠርም ሆነ በከተማ የብዝሀ ልማት ዘርፍን ማጠናከር፣ በግብርና ልማት ዘርፍ እምርታዊ ለውጥ ማምጣት፣ ቢያንስ ከውጭ ወደውስጥ የስንዴ ምርትን የማያስገባ የግብርና አቅም መገንባት፣ የማዕድን ሀብታችንን አሁን ካለበት ወደፊት እንዲስፈነጠር ማድረግ፣ የኢንዱስትሪንና የቱሪዝምን እድገት ሊያረጋግጡ የሚችሉ አማራጮችንና ዘዴዎችን መከተል እንዳለብን ጉባኤያችን አጽንኦት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡

ስለሆነም የብልጽግና ፓርቲ የመጀመርያው ጉባኤ እስከሚቀጥለው ጉባኤ ድረስ መሳካት አለባቸው ብሎ ባስቀመጣቸው የልማት አጀንዳዎች ላይ ቀን ከሌት ተረባርቦ ተስፋ ሰጭ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለበት መተማመን ላይ ደርሰናል፡፡ ለተግባር ስኬታችንም ቃል እንገባለን፡፡

5ኛ. የአገራችንን ሉአላዊነት እንደወትሮው ሁሉ ለማረጋገጥ ዝግጁ ነን፡፡ ምንም እንኳን ከውስጥም ከውጭም የሚፈታተኑን ኃይሎች በርካታ ቢሆኑም ማንኛውንም ጥቃት መቋቋም የሚችል የውስጥ አቅም ለመፍጠር እየተረባረብን እንገኛለን፡፡
በተለይም ጦርነትንና ግጭትን የሚያስቀር ጠንካራ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ስራ መስራት እንዳለብን ጉባኤያችን በአንክሮ ተመልክቶታል፡፡

የታላቁን ህዳሴ ግድብ ማጠናቀቅ አንድ አገራዊ ወሳኝ ተልዕኳችን ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ብዥታዎችን ያለማመንታት መቅረፍ እንዳለብን እናምናለን፡፡ ለጎረቤት አገሮች የምንሰጠውን ልዩ ትኩረት አጠናክረን በመቀጠል የቀጠናውን ትብብር ማሻሻል እና የኢትዮ ኤርትራን ግንኙነት የበለጠ ማጽናት አለብን ብለን እናምናለን፡፡

ድህረ ጦርነት ሰላምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የትግራይን ህዝብ ጨምሮ የመላውን ህዝባችንን ማህበራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ ሳንታክት እንሰራለን፡፡ ዜጎች በርሀብና በድርቅ እንዳይጎዱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ኢትዮጵያዊ ወንድማማችንትንና እህትማማችነትን ማጎልበት፣ እርስ በእርስ የመረዳዳት ባህላችንን ከፍ ማድረግ፣ አንዳችን ለሌላችን ያለንን ፈጥኖ ደራሽነት ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡

ስለሆነም በጦርነትና በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በቅድመ ጥናት እና በጥንቃቄ ላይ ተመስርተን ወደየቀያቸው የሚመለሱበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ለህዝባችን ሰላማዊ አኗኗር ስረ ምክንያት የሆኑ የሽብር፣ የጽንፈኝነት እና የማን አለብኝነት ዝንባሌዎችን በእንጭጩ እየቀጨን የህዝባችንን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል እንዳለብን እናምናለን፡፡

በሁሉም አካባቢ የወደሙና የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት አለም አቀፍ ጫናን ተቋቁሞ ሉአላዊነትን የሚያጸና ዲፕሎማሲያዊ አቅጣጫዎችን ለመከተል አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ አለብን፡፡

6ኛ. የሀገራችን ፖለቲካ ለህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ባለው ፋይዳ ልክ መቃኘት አለበት፡፡ አገራዊ አንድነትን የሚያጸና፣ አብሮነትን የሚያጎለብት፣አገር በቀል እሴቶቻችንን ለላቀ ጥቅም የሚያውል፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን የሚያቀል እንዲሆን መስራት ይኖርብናል፡፡ ከዚህ አኳያ ጠንካራ የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን ስራ መስራት አለብን፡፡

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታችንን በማጠናከር የአንደኛውን ህመም ሌላኛው የሚጋራበት፣ በሌላኛው ጫማ ላይ ቁሞ ቁስልን የሚረዳበት እርስ በእርስ የመተጋገዝ፣ የመከባበር እና የመቻቻል ዘመናዊ የፖለቲካ ባህል መገንባት አለብን ብለንም እናምናለን፡፡
ዴሞክራሲን እየናፈቅን ዴሞክራሲ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለመክፈል የማንፈቅድ ከሆንን ዴሞክራሲ በዘፈቀደ አይገኝም፡፡

ብልጽግናን እና የህዝባችንን ኑሮ መሻሻል እየተመኘን ነገር ግን ሁሉ ነገራችን ፖለቲካ ብቻ ከሆነ ያሰብነው አይሳካም፡፡
ሰላምና ጸጥታን እየፈለግን ነገር ግን በየመንገዱ ለጸብ፣ ለክርክርና ለጥላቻ መሰረት የሚሆን ስድብ፣ ዘለፋ፣ ስም ማጥፋት እና አብሪተኝነትን የምናስቀምጥ ከሆነ ሰላም በምኞት ብቻ ሊሳካ አይችልም፡፡ ስለሆነም በማህበራዊ ድረገጽ ትስስርም ሆነ በሁሉም የሚዲያ አማራጮች ዘወትር የምንናፍቀው የህዝባችን ሰላም እና የአገራችን አንድነት እንዲሳካ መረባረብ አለብን፡፡

በመጨረሻም የብልጽግና ፓርቲ የመጀመርያው ጉባኤያችን በመከረባቸው በሁሉም ጉዳዮች ላይ አጽንኦት ሰጥቶ አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን ለህዝባችን ሁለንተናዊ ሰላም ደህንነት እና ተጠቃሚነት መረጋገጥ በፍጹም ቁርጠኝነት የምንሰራ መሆኑን እያረጋገጥን ጉባኤያችን በታላቅ ስኬት የተጠናቀቀ መሆኑን ለመላው ህዝባችን እናበስራለን፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለብልጽግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች፣ ለሁሉም የእምነት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ለአገራችን አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች፣ ለምሁራን እና ለንግዱ ዘርፍ የማህበረሰብ አባላት፣ ለባለሀብቶች፣ ለወጣቶች እና ለሴቶች፣ አገራችሁን በተለያዩ መስኮች ለምታገለግሉ ውድ ኢትዮጵያውያን፣ ለአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት እና በፌዴራል፣ በአዲስ አበባ ፣ በድሬዳዋና በሁሉም ክልሎች የምትገኙ የፀጥታ አባላት፣ በውጭ አገር ለምትገኙ የዲያስፖራ አባላት ፣ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ አገር የሚጸናው፣ የሚያድገው እና የሚበለጽገው በሁሉም ዜጋ የጋራ እርብርብ ነው በሎ ፓርቲያችን ብልጽግና ያምናል፡፡ ስለሆነም እናንተን ሳንይዝ የምናሳካው አንዳችም ነገር ስለሌለ በሁሉም መስክ የተለመደውን አገራዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እያስተላለፍን ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት መከበር፣ ለህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት በጋራ እንድንቆም የአደራ መልዕክታችንን ስናስተላለፍ በታላቅ አክብሮት ነው፡፡

ብዝሃነት ጌጣችን ኢትዮጵያዊነት መገለጫችን ነው !!!
መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ

“በዋጋ ጭማሪና በኑሮ ውድነት ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ የምግብ ፍጆታዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን።” የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ


በተለይም በከተማ አስተዳደራችን ውስጥ በመንግስት ድጎማ እየተሰራጨ ያለውን የምግብ ዘይትና ዳቦ በተመለከተ ልዩ ትኩረት ሰጥተናል።

የምግብ ዘይት በህገወጥ ክምችት የተገኘውንም ጨምሮ በተለያዩ አቅራቢዎችም እንዲቀርብ በማድረግ ለጊዜው ከ2 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት እያሰራጨን እንገኛለን፡፡
በመሆኑም የከተማችን ነዋሪ በተለይም በዝቅተኛ ገቢ የምትተዳደሩ በየአካባቢያችሁ ወደሚገኙ የሸማች ሱቆች በመሄድ ምርቶቹን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
የሸገር ዳቦን በተመለከተ ፋብሪካው በእድሳትና በወቅቱ የስንዴ ዋጋ ንረት ምክንያት ለጊዜው ማምረት አቁሞ እንደነበር ይታወቃል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለሸገር ዳቦ 613 ሚሊዮን ብር ድጎማ በማድረግ፣ እንዲሁም በ198 ሚሊዮን ብር ለስንዴ አቅርቦት በድምሩ 812 ሚሊዮን ብር በመመደብ የዳቦ ምርት ማስጀመር ችሏል፡፡

ከነገ ጀምሮም ምርቱ ወደ ገበያ የሚወጣ በመሆኑ ህብረተሰቡ የሸገር ዳቦ በምናሰራጭባቸው ማዕከላት ዳቦ ማግኘት ይችላል።
ነገር ግን እነዚህ ምርቶች ዝቅተኛውንና በተለይም ቅድሚያ ወደሚሰጠው ህዝብ በሚፈለገው ደረጃ መድረስ ላይ እጥረቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ የጀመረው ቁጥጥር ቢኖርም ነገር ግን ህዝቡ በተለይም የዳቦ በመንግስት ከፍተኛ ድጎማ እየቀረበ ሳለ የተሻለ ገቢ ያላቸው የንግድ ድርጅቶችና ባለሃብቶች ምርቱን ወስደው የሚያተርፉበት ሁኔታ እንዳለ መረጃዎች ይጦቅማሉ ፡፡

ህብረተሰቡ ይህንን ሁኔታ በመጠቆምም፣ በማጋለጥም፣ በመቆጣጠርም በኩል ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
የከተማችን የንግዱ ማህበረሰብም በመተሳሰብ ለጊዜው ትርፋችሁን ቀንሳችሁ ህዝባችሁን ታተርፋ ዘንድ በአክብሮት ጥሪ እናቀርብላቹሃለን።

Daballiin gatii dhiibbaa qaala’insa jireenyaa irratti qabu hir’isuuf; nyaata soorataa irratti xiyyeeffannoo kenninee hojjachaa jirra.
Keessummattuu bulchiinsa magaalaa keenyaa keessatti gargaarsa mootummaan kan raabsamaa jiru Zayitii fi Daabboo ilaalchisee xiyyeeffannoo addaa kennineerra.
Zayita seeraan ala kuufamee argame dabalatee iddoolee dhiyoo garagaraatii akka dhiyaatan gochuun yeroof Zayita liitira miiliyoona 2 ol raabsuutti argamna.

Kana ta’uu isaatiin jiraattonni magaalaa keenyaa keessattuu galii gadi aanaan kan bultan Dukkaana raabsitoota naannoo keesanitti argamu deemuun oomishoota argachuu dandeessu.
Daabboo Shaggar ilaalchisee:- Daabboon Shaggar haaromsa warshaa fi sababa daballii gatii qamadiin oomisha dhaabee akka ture ni beekama.

Bulchiinsi magaalichaa Daabboo Shaggariif qarshii miiliyoona 613 gargaarsa gochuun; akkasumas qarshii miiliyoona 198n haaromsa gochuun waliigalatti qarshii miiliyoona 812 ramaduun oomisha Daabboo eegalchiisuu danda’eera.
Kana waan ta’eef oomishni bori irraa eegalee gara gabaatti kan bahu ta’uu fi haaluma wal fakkaatuun hawaasni giddugaloota Daabboon Shaggar itti raabsamuu Daabboo argachuu ni danda’a.

Haata’u malee oomishoonni kun gadi aanaa fi keesaattuu uummata dursi kennamuuf sadarkaa barbaadameen dhaqqabsiisuuf hir’inoonni akka jiran ni beekama. Kanas hir’isuuf bulchiinsi magaalichaa to’annoo jalqabaa jiraatus garuu uummanni keessumattuu Daabboon gargaarsa olaanaa mootummaatiin dhiyaachaa waan jiruuf dhaabbileen daldaalaa galii fooyya’aa qabanii fi abbootiin qabeenyaa oomisha kana fudhachuun kan irraa buufatan ta’uu odeeffannoowwan ni agarsiisu.

Haawaasni haala kana odeeffannoo kennuun, ifa baasuun, to’achuunis gahee isaa akka bahatu waamicha koon dhiyeessa.
Hawaasni daldaalaa magaalaa keenyaas waliif yaaduun yeroof bu’aa keessan hir’isuun akka uummata keessan deeggartan kabajaan waamicha koo isiniif dhiyeessa.

መንግስት የገበያ ስርዓቱን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እንደሚያደርግ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2014

መንግስት ገበያ ስርዓቱን እንደ ቴሌኮም ዘርፍ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እንደሚያደርግ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ተናገሩ፡፡

በየዕለቱ ከቁጥጥር እየወጣ ያለው የዋጋ ንረት የኢኮኖሚ ዕድገቱን ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጓል ተብሏል፡፡

ለዚህም መንግስት የጥቅል ኢኮኖሚ ዕድገት እንዲፈጥር በማድረግ የዜጎችን ገቢ ማሳደግ የሚችልባቸውን አማራጮች ማሰብ ይኖርበታል፤ እስከዛው ግን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ምክንያቱን በለየ መልኩ መፍትሄ እንዲመጣ ከመንግስት ይጠብቃል፡፡

እንደ ገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ገለፃ፥ በዓለም ገበያ የምርቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው፤ አሁን ላይ ላለው የዋጋ ንረት ቀዳሚው ምክንያትም ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ዋጋ በቀጥታ ሸማቹ ላይ እንዲያርፍ መደረጉ ነው፡፡

የአንዳንድ ምርቶች ዋጋ ማለትም በብረት፣ ዘይት፣ ነዳጅና የመሳሰሉት ከውጭ የምናስገባቸው ምርቶች ዋጋቸው እስከ እጥፍ መጨመር በሀገር ቤት ያለው የጸጥታ ሁኔታም በምርት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል የፈጠረና በዋጋ ንረቱ ላይ ትልቅ አበርክቶ አለው ነው ያሉት፡፡

ሌላው መንግስት ወጪውን እየሸፈነበት ያለው የገንዘብ ፖሊሲም በራሱ ጫና የሚፈጥር ነው፤ እነዚህን በጊዜ ሂደት እያስተካከልን መሄድ ካልቻልንም የባሰ ሊመጣ ይችላል ብለዋል፡፡

እነዚህ ሁኔታዎች የራሳቸውን ጊዜ ጠብቀው እንደሚስተካከሉ ይጠበቃል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የጸጥታ ሁኔታው መንግስት ሰላምን በመምረጡ በተሻለ ደረጃ ምርቶች እንዲቀርቡ ዕድል እንደሚፈጥር ይታሰባል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን የሀገሪቱ የገበያ ስርዓት በጥቂቶች ብቻ ያለ በመሆኑ መንግስትን የፈጠነ ማሻሻያ እንዲያስብ እንዳደረገው ተጠቁሟል፡፡
ለዚህም የገበያ ስርዓቱ ለውድድር ክፍት መሆን አለበት ያሉት ዶክተር ዕዮብ ዘርፉ ለውድድር ክፍት ሲሆን፥ 200 በመቶ ካላተረፈ ያላተረፈ የሚመስለው ነጋዴ ወደ ቀልቡ እንዲሰበሰብ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የቴሌኮም ኢንዱስትሪው ለውድድር እንደተከፈተ ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ በቅርቡ ደግሞ የሀገሪቱ የግብይት ስርዓት ለዓለም አቀፍ የንግድ ኩባንያዎች ክፍት እንደሚደረግ ነው ያስታወቁት።

ከእነዚህ ምክንያቶች ባለፈ ግን በዶላርና ብር መሃል ያለው የምንዛሬ ተመን በየጊዜው እንዲሰፋ መደረጉ ለዋጋ ንረቱ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው ተገልጿል፡፡

“የውጭ ምንዛሬ ላይ የጀመርነው ማሻሻያ የጎንዮሽ ጉዳት የለውም የሚል የመንግስት አካል የለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ነገር ግን ሊያመጣ የሚችለውን ተጽዕኖ ተቋቁሞ የሚገኘውን ጥቅም ማሳካት ያስፈልጋል፤ ማሻሻያው መዘግየቱ በራሱ የፈጠረው ተጽዕኖ አለ፤ ያን በፍጥነት ተግብረን ችግሮችን ለመቅረፍ እንሰራለን” ነው ያሉት።

ማሻሻያው በተለይም በወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስገኝቷል ቢባልም ችግሮች በተደራረቡ ጊዜ ግን አንዳንድ ማሻሻያዎችን ማዘግየት እንደ መፍትሄ ይቆጠራልም ነው ያሉት፡፡

በባሃሩ ይድነቃቸው ከ ፋና ቴሌቪዥን

ሀገራዊ ምክክር፤ ለምን?

#Ethiopia #NationalDialogue
(በነስረዲን ሙሃሙድ)

የብሄራዊ መግባባት፣ ብሄራዊ እርቅ፣ ሁሉን አቀፍ ድርድር፣ ወዘተ ጉዳዮች በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር የረጅም አመታት የፖለቲካ ሃይሎች አጀንዳ ሆነው ከርመዋል፡፡ ሆኖም አንዱ ፈላጊና ጠያቂ፤ ሌላው አካል ደግሞ ሰጪና ከልካይ የሆኑበት ስርዓት ተፈጥሮ ስለነበር የሀገርና የዜጎችን ፍላጎት ያሟላ የውይይት መድረክ መፍጠርና መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ግን ስለ ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ ምክክርና ድርድር አስፈላጊነት ገዥው ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከስምምነት ደርሰውበት ተጨባጭ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የብሄራዊ ምክክር መድረኮችን መፍጠር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ፤ በዚሁ መሰረትም መድረኮቹን የሚያደራጅና የሚመራ ተቋም በአዋጅ ተቋቁሟል፡፡ ተቋሙን በበላይነት የሚመሩ ሰዎችም አሳታፊና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ተመርጠዋል፡፡

እዚህ ላይ ብሄራዊ የምክክር መድረኮች በተለይ በዚህ ወቅት ለሀገራችን ለምን አስፈላጊ ሆኑ የሚለውን ጉዳይ በደንብ ማጤን ይገባል፡፡ በእኔ እምነት ኢትዮጵያ እንደ በሁለት አበይት ምክንያቶች የተነሳ የምክክር መድረኮች ያስፈልጓታል፡፡ አንደኛው በሀገራችን የሚስተዋለውን የዴሞክራሲ እጦት ችግርን መፍታት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደቱን ለማሳለጥና ለማፅናት ነው፡፡ እነዚህ እንደ ሀገር የጎደሉን ሁለት ጉዳዮች እርስ በርሳችን እንዳንግባባ በማድረግ ወደ ግጭት አምርተን ለሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት መንስዔ ሲሆኑን ቆይተዋል፡፡

ስለ ዴሞክራሲ ስናነሳ በኢትዮጵያ የብሄሮችና ብሄረሰቦችን መብዛት እንደ እድል ሳይሆን እንደ ስጋት፣ እንደ ጥንካሬ ሳይሆን እንደ የልዩነት ምንጭ የሚወስዱ አሰራሮችን ስንከተል ቆይተናል፡፡ በመሆኑም ልዩነቶችን በብቃት የሚያስተናግድ የዴሞክራሲ ስርዓት መገንባት ተስኖናል፡፡ አብዛኞቹ የሀገራችን የፓለቲካ ፓርቲዎች የብሄር ማንነትን መሰረት አድርገው መደራጀታቸውን እናስተውላለን፡፡ ሆኖም እያንዳንዳቸው የየብሄራቸውን ጥያቄ ከወንድማማችነት ማእቀፍ ውጭ ሆነው ለመመለስ በመሞከራቸው አንዱ የሌላኛውን ሕመም ለመረዳት የማይችልበት የመገፋፋት ፖለቲካ ተፈጥሯል፡፡ የብሔር ጥያቄን ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውጭ ለመመለስ እንደማይቻለው ሁሉ የብሔር ጥያቄ ሳይመለስም ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አይቻልም። ስለሆነም የምናካሂዳቸው ብሄራዊ ምክክሮች አንዱ የሌላውን ወንድሙን ጥያቄና ፍላጎት የሚያዳምጥበትና አብሮ የሚመክርበት፣ ፍላጎትን እያቻቻሉ ለመሄድ የሚያስችል ቅርርብ የሚፈጠርባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን ስናደርግ ነው ስር የሰደደውን የዴሞክራሲ እጦት ችግራችንን ነቅለን መጣል የምንችለው፡፡

ከሀገረ መንግስት ቅቡልነት አኳያ በአሁኑ ወቅት ስራ ላይ የሚገኘውን ህገ መንግስት ብቻውን ነጥለን ብናይ እንኳን እኔን አይወክለኝም ይቀየርልኝ በሚል አንደኛ ወገንና፤ እንከን የለሽ ነውና ንክች እንዳታደርጉት በሚል ሌላ ወገን መካከል ተወጥሮ ሲሳሳብ እናገኘዋለን፡፡ በሁለት ፅንፎች ላይ የተወጠረ ህገ መንግስትን ይዞ ሀገርና መንግስትን ማፅናት አይቻልም፡፡ በሀገሪቱ በሰንደቅ አላማና በአርማው ዙሪያ በየወቅቱ የሚከሰቱና አልፎ አልፎም ለግጭት የሚዳርጉ አለመግባባቶችን እናስተውላለን፡፡ ከክልሎች ወሰን ጋር በተያያዘ የሁለት ሀገራት ህዝቦች እስኪያስመስሉብን ድረስ የሚከርሩ አለመግባባቶች ይፈጠራሉ፡፡ የፌዴራሉ የስራ ቋንቋዎች እንዲሁም አንዳንድ የታሪካችን ትርክቶች የበዳይና ተበዳይ ፅንፍ አስይዘው እንደሚያነታርኩን ይታወቃል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ወደ ውይይት መድረክ ማምጣት፣ የጋራ ድምዳሜ ላይ መድረስና ለተያያዥ ችግሮቻቸው ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ ካልተቻለ የሀገረ መንግስቱን ቀጣይነት ፈተና ውስጥ የሚያስገቡ መሆናቸው አጠራጣሪ አይደለም፡፡

በእነዚህ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እና የሀገረ መንግስት ግንባታ ተደጋጋፊ ጉዳዮች ላይ ተመስርቶ የሚካሄደውን ውይይትና ድርድር በስኬት ማጠናቀቅ ውጤቱ አሁን ላይ ያጋጠሙንን ችግሮች በመፍታት ላይ ብቻ የታጠረ አይሆንም፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያን ከድህነትና ኋላቀርነት በማላቀቅ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያሸጋግር ነው፡፡ እናም መልከ ብዙ ትሩፋቶችን ሊያስገኝልን የሚችለው ብሄራዊ ምክክር ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው በስኬት እንዲቀጥል ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ የድርሻውን መወጣት አለበት እላለሁ፡፡

ከ2008ዓ.ም ጀምሮ በአገራችን የተቀጣጠለው ለውጥ አገራችን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡

ለውጡ የሚመራበት ሁኔታ በሪፎርም ነው ወይስ በሪቮሊሽን መልክ የሚለው ውይይት ተደርጓል፡፡ ለውጡ መመራት ያለበት በሪፎርም ነው በሚለው ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ወደ ተግባር ተግብቷል፡፡ ለውጡ ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ህጋዊ ለውጦችን ያካተተ ነው፡፡

የፖለቲካ ሪፎርምን በተመለከተ የሕዝብ ጥያቄዎች ምን ምን ናቸው፣ አሁን ያለው የፓለቲካ ፍልስፍና የሕዝብን ጥያቄዎች ወደፊት ማራመድ ይችላል ወይ የሚሉ ወሳኝ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተካሄደ ነው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ እያለን ስር ነቀል ለውጥ መምጣት አለበት ተብሎ ወደ ተግባር እንቅስቃሴ ተገብቶ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያም ሪፎርሙን የምንመራበት መንገድ በጥናት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህም ጉዳዩ በማዕከላዊ ኮሚቴ፣ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ታይቶ በገለልተኛ አካላት ዝርዝር ጥናት እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡ በዚህ ጥናት ውጤት መሰረት ሁለት አንኳር ጉዳዮችን ለይቷል፡፡ ከአደረጃጀት አኳይ እና ከፍልስፍና (ከርዕዮተ ዓለም አኳያ) ችግሮች መኖራቸው ተመላክቷል፡፡ ከአደረጃጀት አኳያ የሕዝብን ጥያቄዎች መመለስ አይችልም በሚል ተቀምጧል፡፡ በአገሪቱ እና በፓርቲው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ውጪ አምስቱ አጋር ድርጅቶች በአገራቸው ጉዳይ ተሳታፊ አልነበሩም፡፡ ይህም አግላይ አካሄደው ነበር፡፡ ግለሰቦችም ወደ ፓርቲ አባል ለመቀላቀል ቢፈልጉም የግድ የብሄር አባል መሆን የሚጠይቅ ነበር፡፡

ሁለተኛው ችግር የፍልስፍና (ርዕዮተ ዓለም) አኳያ ሕዝቡን ወደ ለውጥ ሊያራምድ አልቻለም፡፡ ይህም ፓርቲው ጠላትና ወዳጅ ብሎ በመፈረጅ በመሆኑ የኢትዮጵያን ብዙሃነትና አንድነት የማይመጥን ነው ብለዋል፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የመግባባት ዴሞክራሲ መሆኑን በማመን ብልጽግና እንዲወለድ ሆኗል፡፡ የመግባባት ዴሞክራሲ የሽግግር ጊዜ ዴሞክራሲ ነው፤ በፓርቲዎች መካከል ወድድር እንዲኖር ዕድል የማይሰጥ በመሆኑ ትችት ይቀርብበታል፡፡ ሆኖም ፓርቲዎች አለኝ የሚሉትን ሀሳብ ወደ መድረክ በማምጣት በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ ስምምነትና ውይይት የሚካሄድ ሲሆን ባልተግባባንባቸው ጉዳዮች ላይ ወደ ሕዝብ ተመርተው በሕዝብ ውሳኔ ያገኛሉ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ሁለት ዋና አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ የመትከል እንዲሁም ልማትና ሁሉን አቀፍ ብልጽግና በሁሉም ዘርፎች የማረጋገጥ አበይት አጀንዳዎች ናቸው፡፡ እንደብልጽግና ኢትዮጵያን ወደ ገናና ክብሯ የመመለስ ስራ እየተሰራ ነው፡፡

አቶ ብናልፍ አንዷለም
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል

“ለአገራችን የሚመጥን አየር ኃይል ለመገንባት ብዙ ተለፍቷል፤ ይቀጥላል” – ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ

“ለአገራችን የሚመጥን አየር ኃይል ለመገንባት ብዙ ተለፍቷል፤ ይህም ጥረት ይቀጥላል” ሲሉ የአየር ኃይል ዋና አዛዥና የአድዋ ድል ጀግና ከፍተኛ ሜዳይ ተሸላሚ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

አየር ኃይል የላቀ የግዳጅ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አባላትና አመራሮች የሜዳሊያ የማዕረግ ማልበስ መርሃ ግብር አካሂዷል።

በወቅቱ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ እንደተናገሩተት በሕወሓት ዘመን ለ27 ዓመታት አየር ኃይል ወደኋላ እንዲጓዝ ተደርጓል። አሁን ግን በሰው ኃይልም ሆነ በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራው ተጠናክሯል።

ለአገራችን የሚመጥን ጠንካራ አየር ኃይል ለመገንባት ብዙ ተለፍቷል፤ ይህም ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በህዳሴ ግድብ የተገኙ ስኬቶች ለብልፅግና ጉዟችን አቅም ናቸው! #GERD


(በፈድሉ ጀማል)
የህዳሴው ግድብ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት በመጀመር የአባይ ወንዝ ለሀገራችን ያለውን ዘርፈ ብዙ እምቅ አቅም ሳንጠቀምበት በመቅረታችን ለዘመናት ለቆየው ሀገራዊ ቁጭት ምላሽ መስጠት ጀምሯል፡፡ የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ለዚህ ደረጃ የደረሰው በበርካታና ውስብስብ ተግዳሮቶች ውስጥ አልፎ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን ተፈጥሮ የቸረችንን ሃብት እንዳንጠቀም በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ወጥመዶች አስረውን ቆይተዋል፡፡ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መፈፀም የሚችል ኢኮኖሚ አለመገንባታችን፣ የተረጋጋ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አለመፍጠራችን እና ብቃት ያለው አመራር አለማግኘታችን በውስጣችን ያሉ የራሳችን ድክመቶች ናቸው፡፡ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ግብፅ ለግድቡ ግንባታ የሚያስፈልገንን ብድርና ርዳታ እንዳናገኝ፣ አለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች እንዲበረቱብን በማድረግና አለፍ ሲልም የውስጥ ግጭቶችን በመደገፍ ትልቅ አስበን ትልቅ የመስራት አቅማችንን አሳጥተውን ኖረዋል፡፡

ከዘመናት ቁጭትና ፀፀት በኋላ አባይን በራስ አቅም ማልማት ስንጀምርም ፈተናዎቹ ገዝፈው ፊታችን ተደቅነውብን ነበር፡፡ በሀገር ውስጥ በጥቅም ሰንሰለት የተሳሰሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ለፕሮጀክቱ ተብሎ ከእያንዳንዱ ዜጋ የተሰበሰበውን ገንዘብ በማንአለብኝነት በመዝረፋቸው የግንባታ ሂደቱን ትልቅ አደጋ ውስጥ ከተውታል፡፡ ግድቡ በሚገኝበት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልና በሰሜኑ ኢትዮጵያ የተካሄደው ጦርነትም ያሳረፉት ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህን እንደ ምቹ አጋጣሚ የወሰዱ የውጪ አካላት ከግብፅ እስከ አሜሪካ የደረሰ በርካታ ሀገራትንና አለምአቀፍ ድርጅቶችን ያካተተ ሁሉን አቀፍ ተፅዕኖ በማሳረፍ ከጀመርነው የእድገት ጉዞ ሊያስተጓጉሉን ሞክረዋል፡፡

ታላቁን የህዳሴ ግድብ ከመገንባት ጋር ተያይዞ እየተስተዋሉ ያሉ ውጫዊ ጫናዎች ተገቢነት ባይኖራቸውም የሚጠበቁ ግን ናቸው፡፡ ምክንያቱም የዚህ ፕሮጀክት ፋይዳ ውሃ ገድቦ ኃይል በማመንጨት ከሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የዘለለ ስለሆነ ነው፡፡ እንደሀገር በራስ መተማመንን በማሳደግ ለተጨማሪ ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶች የሚያነሳሳ እና በዲፕሎማሲው መስክም ቀጠናዊ፣ አህጉራዊና አለማቀፋዊ ጫና ፈጣሪ የመሆን እድልን የሚፈጥርልን በመሆኑ ነው፡፡

እነዚህ ተግዳሮቶች አሁን ባላቸው መልክ ወይም በሌላ ገፅታቸው በግድቡ ቀሪ ስራዎች ጨምሮ እንደሀገር በምናደርጋቸው ሌሎች የእድገትና የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ሊገለጡ ይችላሉ፡፡ ስኬታችንን የሚወስነው የተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ ሁኔታ ሳይሆን እኛው ጋር ያለው የሚገጥሙን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ የማለፍ ፅናታችን ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ተፅዕኖ የሚገጥሙ ፈተናዎችን ተቋቁሞ በብቃት ማለፍና እያደገ የሚሄድ ሀገራዊ ተጋላጭነትን የመቋቋም አቅም መፍጠር ነው፡፡

ሀገራዊ አንድነታችንን ካጠናከርን፣ ለግድቡ የምናደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ከቀጠልንና አሉታዊ የውጪ ጣልቃ ገብነቶችን በተቀናጀና ብቃት ባለው የዲፕሎማሲ ስራ ከመከተን ፈተናዎቹን እንሻገራቸዋለን፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁን ለሃይል ማምረት ደረጃ የበቃው የትጋታችን ፍሬ ሃይልና ብርታት ይሰጠናል፡፡ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ሳያሸብሩን ተግተን ከሰራን ታላቁን የህዳሴ ግድብ አጠናቀን በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ማስገባት ብቻ ሳይሆን ከሱም የገዘፉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ቀርፀን መተግበር እንችላለን፡፡

ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርግና የኢትዮጵያውያንን ልክ የሚያሳየው ግድብ #GERD

#GERD

ሶስቱ የቀድም ያገራችን መሪዎች የሚከተሉት እሳቤ አይዲዮሎጂ የአመራር ስርዓት የተወለዱበት ከባቢ የተለያየ ቢሆንም ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርግና የኢትዮጵያውያንን ልክ የሚያሳየውን ይሄንን ግድብ ሳያቋርጡ ከሃሳብ እስከ ንድፍ ከንድፍ እስከ ጅማሮ ከጅምሩ እስከ ተግባር ስላስኬዱ ማመስገን ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።

“• አፄ ሃይለ ስላሴ በዚያን ጊዜ ማድረግ የሚያስቸግርም ቢሆን መልካም ሃሳብ መልካም ዘር ለልጆቻቸው ማቆየት እና ቀጣዩ ትውልድ ሊሰራው እንደሚችል አስበውበዚህ ቦታ ላይ ይህንን ፕሮጀክት ዲዛይን አሰርተውቀጣዩ ትውልድ ይገነባዋል የሚል እጅግ ትልቅ ራዕይ በመሰነቃቸው እና ያንን ህልም በልጆቻቸው እውን ስለሆነ ክብር እና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

• አቶ መለስ ዜናዊ በስልጣን ዘመናቸው መጨረሻ አከባቢ ይህ ፕሮጀክት አለም አቀፍ ሁኔታው እና የኢትዮጵያ ሁኔታ ምቹ ጊዜ እንደሆነ አምነው ፕሮጀክቱ እንዲጀመር በማድረጋቸው እና በሳቸው ቆይታ የፕሮጀክቱ እድገት እምብዛም ያላደገ ቢሆንም በማስጀመራቸው እና ከሳቸው የሚቀጥሉ አመራሮች እንደሚጨርሱት ተማምነው ለጀመሩት ስራ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

• አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ፕሮጀክቱ በጅምር በቁፋሮ ጊዜ ላይ ከነበረበት ተረክበው እስከደረሰበት ደረጃ ድረስ ለማድረስ በእርሳቸው ጊዜ የነበረው ምቹ ያልሆነው ፖለቲካል አውድ ሳያግዳቸው ላደረጉት ተጋድሎ ከሁሉ በላይ ደግሞ እድለኛ ሆነው ዛሬ ከእኛ ጋር ሆነው ይህንን ድል ለማየት ስለበቁ እጅግ የከበረ ምስጋናና አድናቆት እንዲሁም እንኳን ደስ ያሎት ልላቸው እወዳለሁ፤

• ሶስቱ የሀገራችን መሪዎች የሚከተሉት እሳቤ፣ አይዲዮሎጂ እና የአመራር ስርዓት የተወለዱበት ከባቢ የተለየ ቢሆንም ኢትዮፕያዊያንን አንድ የሚያደርግ እና የኢትዮጵያውያንን ልክ የሚያሳየውን ይህንን ግድብ ሳያቋርጡ ከሀሳብ እስከ ንድፍ ከንድፍ እስከ ጅምማሮ ከጅማሮ እስከ ተግባር ስላስኬዱ ይህ የኢት|ዮፕያ የወደፊት ጉዞ ምልከታ እንዲሆን ስለሚያግዝ ወደኋላ መለስ ብሎ ማመስገን እና ማስታወስ ተገቢይሆናል፡፡ እኛ የጀመሩትን የጨረስን እንጂ ያስጀመርን ስላልሆንን የጀመሩትን አመስግኖ መጀመር ለሚቀጥለው ስራም አጋዥ ይሆናል፡፡” ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ

ከቂም በቀል፣ ከጥላቻና ከደም መፋሰስ የፖለቲካ ባህል ተላቀን የሰለጠነ የፖለቲካ ዘይቤን በመትከል ለቀጣዩ ትውልድ ወንድማማችነትና መተባበርን ሰላማዊ የፖለቲካ ልምምድን ማውረስ ይኖርብናል፡፡

ብዝሃነታችንን በሚያስተናግድ መልኩ ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንን ማጠናከርና ጠንካራ ኢትዮጵያን መገንባት ላይ መረባረብ ለነገ የምንለው ስራችን አይደለም፡፡

ከሚለያዩንና ከሚበታትኑን ነገሮች ይልቅ የሚያስተሳስሩን አንድ የሚያደርጉን ነገሮች እጅግ በርካታ በመሆናቸው ከመነጣጠል ይልቅ መተባበርና ለጋራ ዓላማ በአንድነት መቆም የሚያዋጣን መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በአንድ ወቅት መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ የልሂቃንና ህዝባዊ ውይይቶችን ማድረግና አገራዊ መግባባት መፍጠር ከአስፈላጊነቱም በላይ ለኢትዮጵያዊያን አንድነት መጠንከር ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡

የብሄር፣ የሃይማኖት፣ የባህል፣የቋንቋና ሌሎች በርካታ የማንነት መገለጫዎች ባሉባት ኢትዮጵያ ብዝሃነታችንን እንደ ውበትና እንደ ጥንካሬ ምንጭ በመጠቀም ሁሉም ዜጋ ኢትዮጵያ የእኔ ናት እንዲል አሳታፊና አካታች የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

አገራዊ ችግሮችን እየመከትን አገር ከማሻገር ጎን ለጎን…

በአብዲ ኬ

እርግጥ ነው እንደ አገር ፋታ የማይሰጡ፤ የአገር ህልውና አደጋ ውስጥ የጣሉ፤ እስከ ደም አፋሳሽ ጦርነት ዘልቆ የበርካታ ሰው ህይወት የቀጠፉ፤ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ንብረት ያወደሙ ፈተናዎች ገጥመውናል፡፡

ይህን እንደ አገር የመቀጠልና ያለመቀጠል የህልውና ጥያቄ ውስጥ የከተተንን ጦርነት፤ በፓርቲው አስተባባሪነት በሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ተሳትፎና በአገር መከላከያ ሰራዊታችንና የክልሎች ልዩ ሃይሎችና ሌሎች ጀግና ልጆቿ ተጋድሎ መቀልበስ ተችሏል፡፡ የመጀመሪያ ምዕራፍ የህልውና ዘመቻም በድል ተጠናቋል፡፡ አሸባሪው ሃይልም እንደ ዛተው ኢትዮጵያን ማፍረስ ሳይችል ቀርቶ፤ ተቀጥቅጦ ወደ ኋላ ተመልሷል፡፡ ለአገር ህልውና አደጋ የመሆን አቅሙንም አጥቷል፡፡ ያ ማለት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ሰላማችን አግኝተናል ማለት አይደለም፤ ይህ ሃይልም መተናኮስና ማሸበር ከማይችልበት ደረጃ ደርሷል ማለትም አይደለም፡፡

ለዚህ ደግሞ በአፋር ክልል የተለያዩ ወረዳዎች ላይ የሞከረው ወረራና ንጹሃንን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ማለት እንደ ፓርቲና በእርሱ እንደሚመራ መንግሰት አሁንም ሰፊና ፈታኝ ስራ አለብን ማለት ነው፡፡

ይህን ብዙ ጉልበት፣ ጊዜና ሃብት ከሚበላ ስራና መደበኛ አገር የማልማት ስራ ጎን ለጎን ደግሞ የፓርቲያችን መዋቅር ጤነኝነት ማረጋገጥና የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲን እያጎለበቱ መሄድም እኩል ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በእነዚህ ፈታኝ አገራዊ ተልዕኮ ውስጥ የሚሳተፉ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት የጠራ የርዕዮተ አለም እውቀትና አስተሳሰብ፣ ጠንካራ የፓርቲ ዲስፒሊን እንዲሁም የአልጋይነት ስብዕና ሊኖራቸው ግድ ስለሆነም ጭምር፡፡

በመሆኑም ላለፉት ሶስት ሳምንታት በአገር ደረጃም፤ እንደ ከተማችን የአባላትና አመራር ግንባታ መድረኮች በሁሉም ደረጃ በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ መድረኮቹ ለአባሉና አመራሩ አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታና የአመራርና አባላቶቻችን አሁናዊ ሁኔታ ግልጽ አድርጎ በሚያሳይ ደረጃውን የጠበቀ ሰነድ ላይ ተመስርተው፤ እንደ ፓርቲ የምንከተለው ርዕዮታዊ እሳቤዎች ዙሪያ አባላቱና አመራሩ ያለው እውቀትና የአስተሳሰብ ጥራት፤ የፓርቲ ዲስፕሊንና ተግባራዊ ብቃትና የህዝብ አገልጋይነት ሰሜቱን የፈተሹ፤ ጥንካሬና ጉድለቶችንም የለዩ ነበሩ፡፡

በቀጣይነትም ደረጃቸውን የጠበቁና የፓርቲውን አሰራርና ህገ ደንብ የተከተሉ የፓርቲ ኮንፍረንሶችና ጉባዔዎችን በማካሄድ የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲን የሚረጋገጥባቸውን ሁሉንም ሂደቶች ሳይሸራርፉ መፈጸም አለባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡

ይህ መሆኑ ፈተናዎችን እየመከቱና መደበኛ ስራዎችን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እየፈጸሙ የአገሪቱን ሁለንተናዊ ችግሮች ለመቅረፍ ብሎም የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ጉልህ አስተዋጽዖ አለው፡፡

በጠራ አስተሳሰብ፤ በጠንካራ ስነ ምግባርና የህዝብ አገልጋይነት ስሜት ለአንድ አላማ በጋራ ከቆምን ወደ ብልጽግና የሚወስደን መንገድ ያጠረ ይሆናል እላለው፡፡

ቸር እንሰንብት!!!

Design a site like this with WordPress.com
Get started